ክቡር ሚኒስትር

Wednesday, 31 March 2010 10:43
(ክቡር ሚኒስትሩ ለጤናቸው በእጅጉ ይጠነቀቃሉ፡፡ ዘወትር በ"ጂም" ውስጥ ናቸው፡፡ እዚያው ጂም የተዋወቁት ሰውዬም እንደዚሁ ከጂም አይጠፉም፡፡ በጂም ውስጥ እንቅስቃሴያቸውን ሳያቋርጡ ወሬያቸውን ይኮመኩማሉ)
- እኔስ ደከመኝ ክቡር ሚኒስትር፤ እርስዎ ጠንካራ ነዎት፡፡
- በል አታቋርጥ፤ ትናንት ያነበብኩት መጽሐፍ በድንገት አታቋርጥ ይላል፡፡
- አሀ የአካል ብቃትና ጥንካሬ መጽሐፍ ለማንበብም ጊዜ አልዎት ክቡር ሚኒስትር?
- አለኝ፤ እሱ ብቻ አይደለም፤ በጎግል ውስጥ ገብቼም ስለዳይት ብዙ አነባለሁ፡፡ የአመጋገብ ሥርዓቴንም "ዳየት" ማለቴ ነው ለማስተካከል እየሞከርኩ ነኝ፡፡
- ሰዉ ግን "ቪ.ኦ.ኤ" ጃም ይደረጋልን ሲሰማ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ነገር የሚያስጠላችሁ ይመስለዋል፡፡
- ቪ.ኦ.ኤ ምን?
- ጃም መደረጉ፡፡
- መቸ ተደረገ? ለነገሩ ሰምቼው አላውቅም፤ ግን እነዚህ ተቃዋሚዎች የሚያወሩትን አትስማ፡፡
- ተቃዋሚዎች አይደሉም፣ኮ ያሉት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው፣ ፀረ ሕዝብ ሬዲዮ ጣቢያ ስለሆነ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
- እናደርጋለን ምን?
- "ጃም እናደርጋለን"
- ትቀልዳለህ?
- እውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለነገሩ እኔ አሁን አሁን ሬዲዮና ቴሌቪዥን የሚሉትን ይደብረኛል፡፡ አሁን አሁንማ "ዩ ቲ ዩብ"፣ "ማይ ስፔስ" ስልክ ከሆነም "ስካይፕ" ነው የምጠቀመው፡፡
- እና ይህ የሚባለው ነገርም አልሰሙትም ማለት ነው?
- አልሰማሁም፤ በጉጉት የምጠብቀው ሌላ ነገር እንጂ፤ እንደዚህ ዓይነቱን ወሬ አይደለም፡፡
- ምንድን ነው በጉጉት የሚጠብቁት ክቡር ሚኒስትር?
- "አይፖድ" በሚያዝያ ላይ ይወጣል ተብሎ የለ፤ ጓደኛዬ ወዲያው እንደወጣ ከአሜሪካ ላክልኝ ብዬዋለሁ፡፡
- እህ እኔም ስለ አይፖድ ሰምቻለሁ፡፡ እንዲያውም በቀደም ኢንተርኔት ካፌ ገብቼ ስለሱ ሳነብ አንዱ መጥቶ ብርቱካን ሚደቅሳ ታመመች ብሎ ሲነዘንዘኝ ትቼው ወጣሁ፡፡
- ዘመድህ ሲታመምማ አብረህ ተጨነቅ እንጂ፡፡
- ማን ዘመዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ብርቱካን ነው ያልኩት ብርቱካን ሚደቅሳ፡፡
- ኧረ እስቲ አንድ ነገር ልጠይቅህ እነዚህ ኢንተርኔት ካፌዎች "ፋስት" ናቸው፡፡
- አንዳንዶቹ ብሮድባንድ ናቸው፡፡ ዋየርለስ ኮኔክሽን ያላቸው አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ተራ "ዲያልአፕ" ናቸው፡፡
- እኔ ኢቪዶ (EVDO) ነው የምወደው፡፡
- እርስዎ እንዴት ስለዘመናዊ ነገሮች እንዳወቁ ገርሞኛል፡፡
- አያመልጠኝም፡፡ ጓደኞቼም አዳዲስ ነገር ሲኖር "ፎርዎርድ" ያደርጉልኛል፡፡
- የኔ ጓደኞቼም ፎርዎርድ ያደርጉልኛል ብዙ ነገር". እንዲያውም ትናንት ማታ ጋዜጠኞች ሊከተሉት ስለሚገባ የምርጫ ሥነ ምግባር ደንብ ልከውልኛል፡፡
- የሥነ ምግባር ኮሚሽን ያወጣው ነው?
- ማን ነው የሥነ ምግባር ኮሚሽን፤ ክቡር ሚኒስትር?
- ይቅርታ፤ ይቅርታ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማለቴ ነው፡፡
- የምርጫ ቦርድ ያወጣው እንጂ፡፡
- የምርጫ ኮሚሽን ምን አወጣ?
- የምርጫ ኮሚሽን ሳይሆን የምርጫ ቦርድ
- ዋት ኤቨር
- ክቡር ሚኒስትር "ቢዚ" ስለሆኑ ነው መሰለኝ፤ አንዳንድ የአገራችን ሁኔታ የማይከታተሉት?
- በጣም፣ በጣም ቢዝ ነኝ፡፡ እውነቴን ነው፤ የማርፈው እዚህ ጂም ስመጣ ብቻ ነው፡፡ ይገርምሃል ባለፈው ለስብሰባ ለንደን ሄጀ ያየሁት ጂም ዋው ጂም ብሎ ዝም ነው፡፡
- አንድ ጓደኛዬ ትልቅ ጂም ሊገነባ ሥራውን ጀምሮ የሲሚንቶ ዋጋ በመናሩ ተወው፡፡
- አትስነፍ፤ በአሉሚኒየም ብቻ ሥራው፤ በሲሚንቶ አታማሀኝ በለው፡፡
- ለአሉሚንየም የሚሆን የውጭ ምንዛሪ የት አለና ክቡር ሚኒስትር?
- ባንክ መጠየቅ ነዋ!
- ባንኩስ የት አለውና ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴ ከቡናውና ከቆዳው ሌላ አሁንማ የአበባ ኤክስፖርት ጨምረንበት የለ እንዴ፤ እንዲያውም አበባ ስል አንድ ነገር አስታወስኩ፡፡ በ"ቫላንታይን ዴይ" ለባለቤቴ አበባ ልገዛላት ከአበባ ሱቅ ውስጥ ገብቼ ያየሁት የአበባ ዓይነት፣ ኢትዮጵያ እንዴት ተለውጣለች አሰኝቶኛል፡፡ እንዲያውም አበባ ብሎ ዝም ነው፡፡
- ርስዎ በሌላ ዓለም ውስጥ ነው የሚኖሩት፣ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት?
- ሌላው ስለ ከሰል፣ ቆሎና ጎመን ሲጨነቅ ይውላል ርስዎ ስለ ሌላ ሌላ ነው፡፡
- ሞደርን መሆንማ አለብን፡፡
- ሁሉም እንደዚያ ቢያስብ ጥሩ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሁሉም ስትል?
- ሁሉም ባለሥልጣን ማለቴ ነው፡፡
- አያስብም ብለህ ነው? የቀለበት መንገድ መሥራት፣ኮ ዘመናዊነትን የመፈለግ ምልክት ነው፡፡
- ነው፤ ግን በቀለበት መንገድ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ይሁን ማለቴ ነው፡፡
- ብቻ ውሎዬ ከሥራ-ጂም-ቤት ". ከቤት--ሥራ-ጂም ነው፤ ኑሮዬ ከሰዎች ጋር ብዙ አላቀላቀለኝም፡፡
- የጋራ ስብሰባ አላችሁ አይደል?
- አዎን አለን፡፡
- እኮ እዚያ ሐሳብ ለሃሳብ ስትለዋወጡ ስለዘመናዊነት ታነሳላችሁ ወይ ማለቴ ነው?
- ውይ ውይ አሁንስ ደከመኝ፤ ትንሽ ልረፍ፤ እንዲያውም "ሻወር" ልውሰድ፡፡
- እኔም በቃኝ ክቡር ሚኒስትር፤ ነገ አገር ውስጥ ገቢ እየተጣለሁ ስለምውል፣ በጊዜ ሄጄ ልተኛ፡፡
- ለምን ትጣላለህ?
- በታክስ ነዋ፡፡
- እንዲያውም ካናዳ፣ኮ ታክስ ራሱ "ሃራሞኒ ታክስ" ይሉታል እንጂ እንደኛ "ቫት" አይሉትም፡፡ "ሃርሞኒ ታክስ" ስሙ ደስ አይልም?
- ስሙማ ደስ ይላል፡፡
- በል በል ሻወር ልውሰድ ቻው፤ በዚያው ቤቴ መሄዴ ነው፡፡
- ቻው ክቡር ሚኒስትር፡፡
(ክቡር ሚኒስትር ቤት ደረሱ፤ ባለቤታቸው በሳሎን ተቀምጠው ቴሌቪዥን ይከታተላሉ)
- ላኩልን እንዴ?
- ምንድን ነው የሚልኩልን?
- የሠርጋቸውን ቪዲዮ ነዋ፡፡
- ለምን ጠየቅክ?
- በጥሞና ስትከታተይ ነዋ ቴሌቪዥን እንደዚህ ስትከታተይ አይቼሽ አላውቅም፡፡ ያውም የእኛ ቴሌቪዥን፡፡
- የናንተውን ጣጣ እየሰማሁ ነዋ፡፡
- ምን የእኛ ጣጣ?
- የፓርቲዎች የክርክር መድረክ ነው የምትሉት?
- እ" እሱ ነው እንደዚህ ያሳሰበሽ?
- የአገሬ ጉዳይ እያሳሰበኝ ስለመጣ ነው፡፡
- ምንም የሚያሳስብ የለም፡፡
- አንተ አታስብም፤ እኔ ግን አስባለሁ፡፡
- ሚኒስትር ስለ አገሩ አያስብም?
- አንተ አታስብም፤ አንዳንዴ፣ኮ ግርም ይለኛል፡፡
- ለምንድን ነው የሚገርምሽ?
- ምን አይተው አንተን ሚኒስትር እንዳደረጉህ አይገባኝም፡፡
- የማልሆንበት አንድ ምክንያት አቅርቢ?
- በየዕለቱ በአገር ውስጥ ስለሚደረገውና ስለሚነገረው ነገር እንኳ አታውቅም፡፡
- እኔ ጋዜጠኛ አይደለሁ፣ ቃል አቀባይ አይደለሁ፡፡
- ቃል ባታቀብልም፣ኮ ቃል መቀበል አለብህ፡፡
- ቃል የምቀበል ወሬኛ አይደለሁማ፡፡
- ፓርቲህ ምን እያለ እንደሆነም ማወቅ አትፈልግማ፡፡
- ፓርቲዬ ምን እንደሚልማ ከፕሮግራሙ አውቀዋለሁ፡፡
- ከጂም ፕሮግራም በላይ የፓርቲህ ፕሮግራም የምታውቅ አይመስለኝም፡፡
- የማላውቀው ነገረኛነትን መጀመርሽ ነው፡፡
- እሺ በቃ፡፡
- ምነው ተናደድሽ?
- ይኸውልህ፣ ሁሉም አሁን በኢትዮጵያ ላይ ተረባርቧል፡፡
- ምን እያለ?
- ሰብዓዊ መብት ተጣሰ፤ ተቃዋሚዎች ታፈኑ፤ መገናኛ ብዙኀን ተሸማቀቀ፤ ታፈነ፤ ርዳታ የመሣርያ መግዣ ሆነ፤ ወዘተ. ምን የማይሉት አለ፡፡
- ለሁሉም መልስ የሚሰጥ አለ፤ አትጨነቂ፡፡
- መልስ አሰጣጡም፣ኮ ቅጥ የሌለው ሆነ፡፡
- ውድ ባለቤቴ እንዴት ነው ቅጥ የሌለው የሆነው?
- "ክቡር ሚኒስትር"፣ መልሳችሁ እኮ አዎን ጂም እናደርጋለን የሚል ሆነ፡፡ መልስ ሰጠን ብላችሁ ላልሰማው ታሰማላችሁ፡፡ እነሱ ስለ ሰብዓዊ መብት በኢንተርኔት ያሰራጩትን እናንተ በቴሌቪዥን ታስተጋባላችሁ፡፡
- አትጨነቂ፡፡
- በቃ አንተ ኃላፊነት ተሰጥቶህም ትንሽ አይከብድህም?
- አይከብደኝም፡፡
- እንዴት አይከብድህም? አገር ሲወቀስ ሲወነጀል?
- "ግመሉ ይጓዛል፤ ውሾቹ ይጮሃሉ" ይባል የለ፡፡
- ነገ፣ "ግመሉ ይጓዝ ነበር፤ ውሾቹ ግን ነክሰው አቆሰሉት" ቢባልስ?
- ለማቁሰል ጥርስ ያስፈልጋል፡፡
- ሊያቆስሉ አስበው ነበር፤ ብላችሁ ስትከሱ አልነበረም ወይ?
- "ነበር" ሌላ፣ "ነው" ሌላ፡፡
- እሺ ካላችሁ እሺ፡፡
- ለመሆኑ ክርክራቸው ጥሩ ነበር?
- ጥሩ ቢሆን ኖሮማ ባልተጨነቅኩ ነበር፡፡
- የማትጨነቂበት ዘዴን አስቢ፤ ፍጠሪ፡፡
- መከተሉን ስለማልፈልግ እንጂ፤ ዘዴው፣ኮ ቀላል ነው፡፡
- ምን የሚሉት ዘዴ ነው?
- "ገደል ግቡ" የሚል ዘዴ፡፡
- ለምን ገደል ግቡ ትይናለሽ?
- ገደል ግቡ ስለምትሉን ነዋ!
(ነገሩ ደስ አላላቸውም፤ ከመኝታ ቤት ገቡ፡፡ ጥዋት ተነሥተው ቢሮ ሲገቡ አስቸኳይ መልዕክት ከፀሐፊያቸው ተሰጣቸው)
- እስቲ ስጪኝ የምን አስቸኳይ መልዕክት ነው፡፡
- ይኸው (ፀሐፊዋ የታሸገው ፖስታ ሰጠቻቸውና ወጣች)
- እ... እንዴ... እ... እንዴ... እኔ እንደዚህ አልኩ እንዴ... እ... ኧረ እኔ እንደዚህ አላደረግኩም". እ (ክቡር ሚኒስትሩ አነበቡ አነበቡና ወደ ላከላቸው አካል ስልክ ደወሉ)
- ሀሎ፡፡
- አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንድ አስቸኳይ መልዕክት ደርሶኝ እያነበብኩት ነው፤ እንዲያውም ጨርሸዋለሁ፡፡
- እንግዳውስ መልሱን በአስቸኳይ ያዘጋጁና መጥተው ማብራርያ ይሰጣሉ፡፡
- እ...
- ይኸውልዎት ክቡር ሚኒስትር፤ ይህ የእኛ ወይም የእኔ መመርያ ወይም ትዕዛዝ አይደለም፡፡ ጥብቅ ትዕዛዝ ተብሎ ከበላይ የመጣልዎት ነው፡፡ ነገ ጥዋት ለጽሑፍም ሆነ ለቃል ማብራርያም ተዘጋጅተው ይምጡ፡፡
- እሺ፡፡
(በተባለው ሰዓት በተባለው ቦታ መልሳቸውን በጽሑፍ አዘጋጅተው ከሰጡ በኋላ የቃል ማጣርያና ማብራርያ፣ ጥያቄና መልስ ለበላይ አካል መስጠት ጀመሩ)
- ስለተሰጠህ ሥልጣን ኃላፊነት በዝርዝር ተሰጥቶህ ነበር?
- አዎን፡፡
- በዚያው መሰረት እየፈጸምክ ነውን?
- እ... በተቻለኝ መጠን እየሞከርኩ ነኝ፡፡
- ለሥራህ የሚጠቅምህ አስፈላጊ እውቀት እንድትቀስም አሜሪካ ለሁለት ሳምንታት ተልከህ ነበር፡፡
- አዎን፡፡
- የሚጠበቅብህን ፈጸምክ? እንድትሄድ የተፈለገው ቦስተን፣ ኒውዮርክና ዋሽንግተን ነበር፤ አንተ ግን ሆሊውድ ማለት፣ ሎስ አንጀለስ፣ ከዚያም ላስ ቬጋስ ሄድክ በሕዝብ ገንዘብ በሕዝብ ጊዜ ቀለድክ፡፡
- መልስ አለህ?
- የለኝም፡፡
- ለንደን ሄደህ ምን እንደምታደርግና ስብሰባም የት እንደምታደርግም በግልጽ ተነግሮህ ነበር፡፡
- አዎን፡፡
- አንተ ግን ስታንፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ገብተህ፣ የኢንተር ሚላንና የቸልሲን የእግር ኳስ ጨዋታ ታይ ነበር፡፡
- ሰውዬው ትኬት ሲገዙልኝ ገባሁ፤ አዎን ስህተት ነው፡፡
- የውጭ ድርጅቶችን ስታገኝ ማቅረብ የሚገባህ መከራከርያ ነጥብና መጠበቅ ያለብህ ምስጢርም በግልጽ መመርያ ተነግሮህ ነበር
- አዎን
- በመጨረሻው ግን እንኳን አገርህን ወክለህ ልትከራከርና ምስጢር ልትጠብቅ ጭራሹንም የአገርን ምስጢራዊ ሰነድ አሳልፈህ ሰጠህ፤ ሽጠህም መጣህ፡፡
- እንመልስልሃለን ብለው ነበር የወሰዱት፤ ኦርጂናል ሳይሆን ፎቶ ኮፒውን ነበር የሰጠኋቸው፡፡
- ቁም ነገሩ ወረቀቱ የያዘው ምስጢር እንጂ፤ ፎቶ ኮፒ መሆኑ አይደለም፡፡ የተባልከው የአገር ይዘትና ምስጢር ሸጠሃል ነው፡፡
- እ...
- እንደሸጥክ ማስረጃ ትፈልጋለህ? ወይስ ማስረጃ እንዳለ አንተም ታውቀዋለህ?
- ይቅርታ አጥፍቻለሁ፤ እንዲያውም እኔም ከነሱ ሊስት ውስጥ መግባት እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡
- የምን ሊስት?
- ከምርጫ በኋላ ከስልጣን ከሚነሡት ሚኒስትሮች ሊስት፡፡
- ከሊስት ውስጥ ገብተሃል... ግን ከሚነሡት ሊስት አይደለም፡፡
- ከምን ሊስት ነው ታዲያ?
- ከሚታሰሩት
ሪፖርተር
No comments:
Post a Comment