Opinion depot


ዓይን

በዳንኤል ክብረት


አንድ የአትክልት ቦታ የነበረው ሰው ነበረ፡፡ ሰውዬው የአትክልት ቦታው አስጠላውና ለመሸጥ ፈለገ፡፡ ከዚያም ወደ አንድ የታወቀ ባለ ቅኔ ዘንደ አመራ፡፡ «የአትክልት ቦታዬን መሸጥ እፈልጋለሁ፤ ገዥዎች እንዲመጡልኝ አንተ እባክህን ማስታወቂያውን ሥራልኝ፡፡ ነገር ግን እባክህ ያለውንም አታስቀር፣ የሌለውንም አትጨምር» ብሎ ጠየቀውና በዋጋ ተስማሙ፡፡ የአትክልት ቦታው ባለቤትም ለታወቀ ጋዜጣ የማስታወቂያውን ሂሳብ ከፍሎ ሄደ፡፡ ባለቅኔውም ወደ አትክልት ቦታው ሄዶ እየተዘዋወረ ሳይቀንስም፣ ሳይጨምርም አየው፡፡
በሳምንቱ ያንን የአትክልት ቦታ በተመለከተ ባለቅኔው ማስታወቂያውን ሠርቶ በተከፈለበት ጋዜጣ ላይ እንዲህ ሲል አወጣው፡፡
«ፀሐይ በምሥራቅ ስትወጣ ብርሃንዋን ያለ ሃሳብ የምታስተኛበት፣ ማታ በምዕራብ ስትገባ ደግሞ ጨረሮቿን የምትሰበስብበት፤ ከዳር ሆነው መስኩን ሲያዩት አዳም ጥሎት የወጣውን ገነት የሚያስታውስ፤ የነፋሱን ለስላሳ ሙዚቃ ተከትለው ዛፎቹ ከወገባቸው በላይ ሲዘናፈሉ በታወቀ የሙዚቃ ባለሞያ የሚሠለጥኑ ወጣት ሙዚቀኞችን የሚመስሉበት፤ ከቀኝ በኩል መንጭቶ ወደ ግራ የሚፈስሰው ምንጭ በቢራቢሮዎች እና በንቦች ሲታጀብ ከቃና ወይን ቤት የሚፈስስ የወይን ጅረት የሚመስልበት፤ በወንዙ ላይ የሚንፈላሰሱት ዳክዬዎች እና ፔሊካኖች ቡድን እየሠሩ የሚያደርጉት ዋና መላእክት በየነገዳቸው የወረዱ የሚመስሉበት አንድ የአትክልት ቦታ ለሽያጭ ቀርቧል፡፡ በሚከተለው አድራሻ ሄዳችሁ በማየት ግዙ፡፡»
ይህ ማስታወቂያ ከወጣ በኋላ ባለቤቱ ከተዋዋሉት በላይ ለባለቅኔው ብዙ ሺ ብሮች ላከለት፡፡ ባለቅኔውም በሰውዬው ደግነት ተገርሞ ተቀበለ፡፡
ከብዙ ወራት በኋላ ባለ ቅኔውና የአትክልት ቦታው ባለቤት ሻሂ ቤት ውስጥ ተገናኙ፡፡
«እንዴት ሆነልህ? የአትክልት ቦታህን ሸጥከው?» ብሎ ባለ ቅኔው ጠየቀው፡፡
«አልተሸጠም» አለና ባለቤቱ መለሰ፡፡
«መቼም ያንን የመሰለ ማስታወቂያ ሳልጨምርም ሳልቀንስም ሠርቼ ገዥዎችን መሳቡ የተረጋገጠ ነው» አለ ባለ ቅኔው፡፡
«ላለመሸጡ ዋናው ምክንያትኮ ማስታወቂያው ነው» አለው ባለቤቱ ሻሂውን ፉት ብሎ እየሳቀ፡፡
«እንዴት፤ እኮ እንዴት» ባለቅኔው እየጓጓም እየደገጠም የያዘውን የሻሂ ስኒ ቀስ ብሎ አስቀምጦ ወንበሩን ወደ ጠረጲዛው አስጠጋ፡፡
«በጋዜጣ ላይ የወጣውን ማስታወቂያ ሳየው የተጻፈው ስለ እኔ የአትክልት ቦታ መስሎ አልታየኝም፡፡ ያንን ማስታወቂያ ይዤ እንደ ገና ወደ አትክልቱ ቦታ ሄድኩ፡፡ እየተዘዋወርኩ አንተ በጻፍከው መሠረት አየሁት፡፡ እውነትክን ነው፡፡ ምንም ኩሸትም ሆነ ድቅሸት የለውም፡፡ ራሴን ወቀስኩት፡፡ እንዴት እስከዛሬ እንደዚህ አድርጌ አላየሁትም ? ብዬ ተናደድኩ፡፡ በመጨረሻም ይህንን ዓይን የሰጠኸኝን አንተን አመስግኜ ከውለታችን በላይ ብዙ ብር ከፈልኩህ፡፡ የአትክልት ቦታውን መሸጤንም ተውኩት፡፡ ይኼው ነው ምክንያቱ» አለው ባለቤቱ፡፡
የባለቅኔውም ፊቱ በደስታ ፈካ፡፡
«በአንተ እና በእኔ መካከል ያለውን ልዩነት ዐወቅከው? ልዩነቱ ያየነው የአትክልቱ ሥፍራ አይደለም፡፡ ሁለታችንም ያየነው አንድ ዓይነት ቦታ ነው፡፡ ሁለታችንን የለያየን ነገሮችን ያየንበት መንገድ ነው፡፡ አንተ በአትክልት ሥፍራው ውስጥ ለሚገኙት ደካማ ነገሮች ብቻ ትኩረት እየሰጠህ ነበር የምታየው፡፡ እኔ ደግሞ በአትክልት ሥፍራው ውስጥ ያለውን ውበት ነው ያየሁት፡፡» አለው ባለ ቅኔው፡፡
«ልክ ነህ» አለ ባለ አትክልቱ፡፡ «እኔ ወንዙን አይቼዋለሁ፤ ነገር ግን የዳክዬዎቹን እና የፔሊካኖቹን ትርዒት አላየሁትም፡፡ ዛፎቹን አይቻቸዋለሁ፤ ከንፋሱ ጋር ተዋሕደው የፈጠሩትን ውዝዋዜ ግን አላየሁትም፡፡ ለብዙ ቀናት በአትክልት ቦታው ላይ ሆኜ ፀሐይ መቶኛል፡፡ ለመጠለል ዛፎቹ ሥር እገባ ነበር እንጂ እንደ አንተ ግን የጨረሩን አመጣጥ አላየሁትም፡፡ እኔ ያየሁት ለአትክልቱ የማወጣውን የጥበቃ፣ የአትክልተኛ እና የኪራይ ገንዘብ ብቻ ነው፡፡
«ለኔ ያ ቦታ የአትክልት ቦታ ብቻ ነበረ፡፡ ለአንተ ግን የሕይወት እና የውበት ቦታም ጭምር ሆነ፡፡ እኔ የወዳደቁትን የረገፉ ቅጠሎች ስመለከት አንተ ግን የተንሳፈፉትን ሕይወት ያላቸው ቅጠሎች አሳየኸኝ፡፡ እኔ በደረቁ ዛፎች ስበሳጭ፤ አንተ ግን ከደረቅ ዛፍ ላይ ውበት አመነጨኽ፡፡
«እኔ ወንዙ በአትክልት ቦታው መካከል ሲያልፍ ግራ ቀኝ የፈጠረውን ረግረግ እና ጭቃ እንጂ በአወራረዱ ላይ ያለውን ውበት ለማየት አልታደልኩም፡፡ እኔ በየጊዜው እያደገ ካላጨድከኝ የሚለው ሣር አስመረረኝ፡፡ አንተ ግን ሣሩ እንደ ደብተራ ጎንበስ ቀና እያለ ሲዘምም አየኸው፡፡ አዲስ ነገር አላመጣኸም፤ አዲስ ዓይን እንጂ፡፡» አለው ባለ አትክልቱ የሻሂውን ጭላጭ አንጠፋጥፎ ሌላ ለማዘዝ አሻግሮ እያየ፡፡
«ድሮምኮ በዓለም ላይ አዲስ ዓይን እንጂ አዲስ ነገር የለም» አለ ባለ ቅኔው በጣቱ ጠረጲዛው ላይ እየጻፈ፡፡
«ዓይን አይደል የለየን» ባለ አትክልቱ ሣቀ፡፡
«እርሱ ብቻ አይደለም» አለ ደግሞ ባለ ቅኔው በሁለት መዳፉ አገጩን ደግፎ፡«የቆምንበት ቦታም ይለያያል፡፡ ከሕይወት ላይ ቆመህ ሞትን ስታይ እና ከሞት ላይ ቆመህ ሕይወትን ስታይ ይለያያል፡፡ ለእውነት የሚሞቱ ሰማዕታት በሞታቸው ቀን ፊታቸው እንደፈካ፤ ገጻቸው እንዳበራ በደስታ የሞትን ጽዋዕ ለምን ይጎነጩታል? ምክንያቱም እነርሱ በሕይወት ላይ ሆነው ሞትን ስለሚያዩት የሞት መከራው ሳይሆን ውበቱ ይታያቸዋል፤ ሐሣሩ ሳይሆን ክብሩ ይታያቸዋል» አንገቱን ወደፊት ሠገግ አደረገ፡፡
«ይተንተንልኝ» አለ ባለ አትክልቱ ተጨማሪውን ሻሂ እያዘዘ፡፡ ባለ ቅኔውም ደገመ፡፡
«አንድን ነገር በፍቅር ላይ ሆነህ እና በጥላቻ ላይ ሆነህ፤ በደስታ ላይ ሆነህ እና በኀዘን ላይ ሆነህ፤ በብርሃን ላይ ቆመህ እና ጨለማ ላይ ቆመህ ስታየው የሚኖርህ ሥዕል ይለያያል፡፡ ውበት ያለውኮ በምታየው ነገር ላይ አይደለም፤ ዓይንህ ላይ ነው፡፡ ልቡናህ ውስጥ ነው፡፡»
«አንድ ነገር አስታወስከኝ» አለ ባለ አትክልቱ፡፡
«አንድ ወዳጅ አለኝ፡፡ እኔ ከሥራ ቦታዬ ወደ ቤቴ ስገባ እርሱን ወደ ውጭ ሲወጣ አገኘዋለሁ፡፡ ነገሩ ሲደጋገምብኝ ጊዜ አንድ ቀን ጠየቅኩት፡፡ ሁሌ ማታ ማታ ከሥራ ወደ ቤት ሳይሆን ከሥራ ወደ መሸታ ቤት ለምን ትሄዳለህ? አልኩት፡፡ ቤቴ አስጠላኝ አለኝ፡፡ በሦስተኛው ቀን አብረን ቤቱ ሄድን፡፡
«የወርቅ ፍልቃቂ የመሰሉ ልጆች አሉት፡፡ ባለቤቱ ትኁት እና ባለሞያ ናት፡፡ የቤት አያያዝዋ ቤቱን ቤተ መንግሥት አስመስሎታል፡፡ የዕቃዎቹ አደራደር ሊቃውንተ የተጠበቡበት እንጂ ብቻዋን ያደረገቸው አይመስልም፡፡ ያቀረበችልን ምግብ ሳትበላው በአቀራረቡ ብቻ ትጠግባለህ፡፡
«ምኑ ነው ቤትህ ያስጠላህ? አልኩት፡፡ ያየሁትን ነገር ስነግረው ስለ እርሱ ቤት የምነግረው አይመስለውም ነበር፡፡ እርሱ ቤቱን እንጂ የቤቱን ዝርዝር አይቶት አያውቅም፡፡ ምሳ መብላቱን እንጂ አቀራረቡን፣ አወጣጡን እና አዘገጃጀቱን አድንቆት አያውቅም፡፡ መጀመርያውኑ ቤቱ ያው ነው ብሎ አምኗል፡፡ ስለዚህም ምንም ነገር አይታየውም፡፡ ለማየት አልተዘጋጀማ፡፡» ባለ አትክልቱ ከሻሂው ተጎነጨለት፡፡
«ለዚህኮ ነው ነገሮችን እንድንጠላ፣ እንድንንቅ፣ እንድናማርር እና እንድንሰለች፣ ከሚያደርጉን ምክንያቶች አንዱ የምናይበት አተያይ ነው የሚባለው፡፡ እኛ የሰለቸንን፣ የምናማርረውን እና ያስጠላንን ቤት ሌሎች መጥተው ሲያዩት ሰፍ ይሉለታል፡፡ ይጓጉለታል፡፡ እኛ አቃቂር የምናወጣለትን እነርሱ ቅኔ ይቀኙለታል፡፡ እኛ የምናሾፍበትን እነርሱ ውዳሴ ያዘንቡለታል፡፡ እኛ ያቅለሸለሸንን እነርሱ ይቀኑበታል፡፡ ልዩነቱ ከአስተ ያያታችን ነው፡፡
«አያሌ ባለትዳሮች ትዳራቸው እና የትዳር አጋራቸው የሚሰለቻቸው በእውነቱ ነገሩ አሰልች በመሆኑ ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ የሚያዩበት ዓይን ጉዳይ ነው፡፡ በቤታቸው ውስጥ ምንድን ነው የሚያዩት? ነው ጥያቄው፡፡ በቤቱ ውስጥ ከሚያናድደው፣ ከሚያስጠላው እና ከሚያስመርረው ነገር ይልቅ የሚያስ ደስተውን፣ የሚያረካውን እና ነፍስን በሐሴት የሚሞላውን ነገር ማየት ለምን አይጀምሩም? ሚስቴ ያው ሚስቴ ናት፤ ባሌም ያው ባሌ ነው ብለውኮ ነው የሚያስቡት፡፡
«አንዳንዶቹማ እነርሱ ያላዩትን የትዳር አጋራቸውን ውበት ሌላው ያየውና መማለል ሲጀምር ነው ያልታያቸውን ውበት ማየት የሚጀምሩት፡፡ ለካ እንዲህ ነበረ ማለት የሚጀምሩት፡፡»
«ምን እርሱ ብቻ» አሉ ባለ አትክልቱ፡፡ «አሁን ሳስበውማ በሀገር ላይ ያለው ችግርም ይኼው ነው፡፡ ለመሆኑ የት ላይ ቆመህ ነው ባህልህን፣ እምነትህን፣ ቅርስህን፣ ማንነትህን፣ ታሪክህን የምታየው? ይኼኮ ወሳኝ ነው፡፡ እስኪ ተመልከት እኛ የምንንቃቸውን፤ አይተናቸው የማናውቃቸውን፤ ከቁም ነገር ያልቆጠርናቸውን ነገሮች ሌሎች ከሩቅ መጥተው መጽሐፍ ጽፈው፣ ፊልም ሠርተው፣ ዘገባ አዘጋጅተው በሚዲያ ሲያቀርቡት እንገረማለን፡፡ እኛ ያላየነውን እኛ እነርሱ ያዩልናል፡፡ የናቅነውን ያከብሩታል፡፡ የጣል ነውን ያነሡታል፡፡
«ችግሩ እንዳልከው የጉዳዩ መኖር አለመኖር አይደለም፤ አተያያችን ነው፡፡ የዓይን ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ለታቦተ ጽዮን ከምንሰጠው ክብር በላይ እነርሱ ለአንድ የጥንት ብርጭቆ ይሰጣሉ፡፡ ለምን? እኛ ራሳችንን በንቀት አምባ ላይ ቆመን ነው የምናየው፤ እነርሱ ግን ራሳቸውን በክብር አምባ ላይ ቆመው ነው የሚያዩት፡

Blog Archive